የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈፃፀም መርማሪ ቦርድ ሥራውን ጀመረ

ኅዳር 9/2014 (ዋልታ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈፃፀም መርማሪ ቦርድ በአዋጁ አፈፃፀም ሂደት ላይ የሚኖሩ የሰብኣዊ መብት ጥሰቶችን ለመመርመር የሚያስችለውን እቅድ አዘጋጅቶ ወደ ሥራ መግባቱን ገለፀ።
ቦርዱ ዜጎች በወንጀል ጥርጣሬ ሳይሆን በማንነታቸው ምክንያት ኢሰብኣዊ ድርጊት ከተፈጸመባቸው ድርጊቱን የፈጸሙ አካላት ወደ ሕግ እንዲቀርቡ እሰራለሁ ብሏል።
የቦርዱ ሰብሳቢ ለማ ተሰማ አዋጁን ባልተገባ መንገድ በመጠቀም በዜጎች ላይ ኢሰብኣዊ ድርጊት እንዳይፈጸም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራን ነው ብለዋል።
ቦርዱ ከኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብቶች ኮሚሽን እንዲሁም ከብሔራዊ አደጋና ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ጋር እየሰራ ስለመሆኑም አስታውቀዋል።
መርማሪ ቦርዱ በቀጣይ በሚያደርገው የመስክ ምልከታ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሕግ ጥላ ስር ያሉ ግለሰቦችን እንደሚጎበኝና በአገሪቱ ባለው ጦርነት ከመኖሪያ ቄያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ያሉበትን ሁኔት እንደሚመለከትም ተገልጿል።
7 አባላት ያሉት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ መቋቋሙ ይታወሳል።
በመስከረም ቸርነት