መንግሥትንና አሸባሪ ቡድንን በእኩል ማዬት ተቀባይነት የለውም- አን ፊትዝ ጌራልድ (ፕ/ር)

ኅዳር 9/2014 (ዋልታ) አሜሪካን ጨምሮ አንዳንድ ምዕራባዊያን አገራት በሕዝብ የተመረጠ መንግሥትንና አሸባሪው ሕወሓትን በእኩል ሚዛን ማስቀመጣቸው ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ድርጊት መሆኑን በካናዳ ዊልፍሪድ ላውሪየር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰሯ አን ፊትዝ ጌራልድ ገለጹ፡፡

ምዕራባዊያን አገራት በኢትዮጵያ ሰላም እንዲመጣ ጽኑ ፍላጎት ካላቸው አሸባሪው ሕወሓት ላይ እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸውም አመላክተዋል።

ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም በተከታታይ ጽሑፋቸው እውነትን እያሳወቁ የሚገኙት አን ፊትዝ ጌራልድ (ፕ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት በሰሜን ዕዝ ላይ አሰቃቂ ጥቃት በመፈጸም ኢትዮጵያ አሁን ለገባችበት የጸጥታ ችግር  ዋነኛ ተጠያቂው አሸባሪው ሕወሓት ነው፡፡

በመሆኑም ይህ ቡድን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ከተመረጠ መንግሥት ጋር የሞራል እኩልነት መስጠት መሰረታዊ ስህተት መሆኑን አስገንዝበዋል።

“በዚህም አሜሪካን ጨምሮ አንዳንድ ምዕራባዊያን አገራት ውግንና ያለውና ሚዛናዊ እይታ የጎደለው አካሄድ እየተከተሉ ነው” ብለዋል።

ይህ የተሳሳተ አካሄድ በኢትዮጵያ ያለውን ግጭት ለመፍታት እንደማያግዝም አመልክተዋል።

“በኢትዮጵያ አሁን ሥልጣን ያለው መንግሥት ከፍተኛ የሕዝብ ድጋፍ ያለው ነው፤ ድምጽ ለመስጠት የወጣው ሕዝብ ቁጥር በቅርብ ጊዜ ዓለማችን ላይ ከተደረጉ ምርጫዎች የሚበልጥ ነው” ብለዋል የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰሯ።

ለግጭቱ መከሰት፣ መራዘምና መስፋፋት እንዲሁም ለዜጎች መከራና ስቃይ ተጠያቂ በሆነው አሸባሪው ሕወሓት ላይ ምዕራባውያኑ እርምጃ አለመውሰዳቸው የተሳሳተ መንገድ እየተከተሉ እንደሆነ ማሳየቱን ገልጸው፤ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫና ማሳደራቸው ተገቢነት እንደሌለው ገልጸዋል።

በአሜሪካ የሚመሩ ምዕራባዊያን አገራት በኢትዮጵያ እየተከተሉት ያለውን ፖሊሲ ዳግም በማጤን ገንቢ ሚና መጫወት እንዳለባቸውም ጠይቀዋል።