በጅማ ከተማ ለሽብር ተግባር ሊውል የነበረ 9 ሺሕ 375 ሲም ካርድን ጨምሮ የተለያየ ቁሳቁስ ተያዘ

ኅዳር 10/2014 (ዋልታ) በኦሮሚያ ክልል ጅማ ከተማ ለሽብር ተግባር ሊውል የነበረ 9 ሺሕ 375 ሲም ካርድን ጨምሮ የተለያየ ቁሳቁስ መያዙን የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።

በከተማዋ አሸባሪዎቹ ሸኔ እና ሕወሓት የሽብር ድርጊት እንዲፈጽሙ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ድርጊት የተጠረጠሩ ግለሰቦችም በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ከሲም ካርዶቹ በተጨማሪ 1 ሽጉጥ፣ 5 ላፕቶፕ፣ ሀሰተኛ መታወቂያ እና የሸኔ አርማዎች ከነ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው እንደሚገኙ የፖሊስ መምሪያው ኃላፊ ኮማንደር ፉፋ መገርሳ ገልጸዋል።

በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል አሸባሪዎቹ ሸኔ እና ሕወሓት የሽብር ድርጊት እንዲፈጽሙ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ድርጊት ተሳትፎ እንዳደረጉ መጠርጠራቸውን ኮማንደር ፉፋ አመላክተዋል።

ይህም ውጤት የተገኘው በተለያዩ የጸጥታና ህዝባዊ መዋቅር፣ ከከተማው ነዋሪ፣ ከአጎራባች ዞኖች፣ ወረዳዎችና ክልሎች ጋር በቅንጅትና በመናበብ በተሰራው ስራ መሆኑን አመልክተዋል።

ከእነዚህ አካላት ጋር በተሰራው ስራም በጅማ ከተማ ባለፉት ስድስት ወራት ከፍተኛ የሆነ የሰላምና የጸጥታ መሻሻል የታየ መሆኑን ገልጸዋል።

የተገኘው ሰላምና ጸጥታ በአስተማማኝ ደረጃ ላይ እንዲደረስ ከተለያዩ አካላት ጋር የተጀመረው መናበብ እና ተቀናጅቶ የመስራት እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ይቀጥላል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ኅብረተሰቡና የጸጥታ መዋቅሩ የተገኘውን ሰላም ወደ ላቀ ደረጃ እንዲደረስ የበኩላቸውን የዜግነትና የሙያዊ ኃላፊነትና ግዴታቸውን እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።