የጋምቤላ ክልል በአፋር እና አማራ ክልል ለተፈናቀሉ ወገኖች አራት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለማድረግ ወሰነ

ኡሞድ ኡጁሉ

ኅዳር 10/2014 (ዋልታ) የጋምቤላ ክልል መንግስት በአፋር እና አማራ ክልል ለተፈናቀሉ ወገኖች አራት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለማድረግ መወሰኑን አስታወቀ።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ የጋምቤላ ህዝብና መንግስት ለአገር መከላከያ ሰራዊትና ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚያደረገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ የገጠማትን ፈተና በድል ለማጠናቀቅ በርካታ ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ የጋምቤላ ክልል ህዝብና መንግስት ለኅልውና ዘመቻው በግንባር እየተዋደቁ ለሚገኙ የሃገር መከላከያ ሰራዊት እና በሕወሓት የሽብር ቡድን ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች የማያቋርጥ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

ሕወሓት በወረራቸው የአማራና የአፋር ክልሎች ለተፈናቀሉ የኅብረተሰብ ክፍሎት 4 ሚሊዮን ብር የክልሉ መንግስት ድጋፍ ለማድረግ መወሰኑን ገልፀው በቅርቡ ለተጎጂዎቹ እንደሚደርስ ጠቁመዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በሰሜኑ የአገሪቱ አካባቢዎች እየተካሄደ ካለው የኅልውና ዘመቻ ባልተናነሰ በመተከል ዞን ሕወሓት ተላላኪ ቡድን ለመደምሰስ ለተሰማራው የክልሉ ልዩ ኃይል 2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ መደረጉንም አብራርተዋል።

መከላከያ ሰራዊቱንና በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉና የተጎዱ ወገኖችን በገንዘብም ሆነ በዓይነት የመደገፉ ስራ በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ርዕሰ መስተዳድሩ ገልፀዋል።

እስካሁን ከ27 ሚሊዮን ብር በላይ በክልሉ ከሚገኙ የመንግስት ሰራተኞች፣ አመራሮች እና ከኅብረተሰቡ በማሰባሰብ ለአገር መከላከያ ሰራዊት መላኩን መናገራቸውን ከክልሉ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።