ኅዳር 10/2014 (ዋልታ) በአሜሪካ ኮሎራዶ የኢትዮጵያ ኮሙዩኒቲ በወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳይ ከሪፐብሊካን ፓርቲ አመራሮች ጋር ዛሬ ውይይት እንደሚያደርግ ገለፀ፡፡
በአሜሪካ የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ኔትዎርክ ሊቀመንበር ማማይ ወርቁ ከዋልታ ጋር በነበራቸው የበይነ መረብ ቆይታ ላለፉት ወራት ከፓርቲው ጋር ውይይት ለማድረግ ጥያቄ ሲያቀርቡ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
በአገሪቱ ተፅዕኖ መፍጠር የሚችለው የሪፐብሊካን ፓርቲ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ይህ ነው የሚባል እንቅስቃሴ አለማድረጉን ተከትሎ ጥያቄውን ስለማቅረባቸው ሊቀመንበሯ ጠቁመዋል፡፡
የውይይቱ ዋነኛ ዓላማም ጥቅምት 24/2013 ምሽት አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በመከላያ ሰራዊት የሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ካደረሰበት ጊዜ አንስቶ በኢትዮጵያ ላይ በከፈተው ጦርነት እስካሁን እየሆነ ያለውን ለፓርቲው አመራሮች ማስረዳት እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
ይህን ተከትሎ በኢትዮጵያ ላይ በተለይ ከአሜሪካ የተከፈተባትን ዘመቻና ያልተገባ ጫናን ለማስቆም ፓርቲው ድምጽ እንዲሆንም እንጠይቃለን ብለዋል፡፡
ሊቀመንበሯ በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለዴሞክራቶች መመረጥ አበርክቷቸው ከፍ ያለ እንደነበር ጠቅሰው ‹‹የባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ ላይ ከሚያደርገው ያልተገባ ጫና በመነሳት ተክደናል በሚል ስሜትና ቁጭት ውስጥ እንገኛለንም›› ብለዋል፡፡
ከዚህ በኋላም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ከጥቅማችን አንጻር እየተደራደርን ድምጻችንን የምንሰጥ ይሆናል ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
በነስረዲን ኑሩ