በአካባቢው ሰላም እንዲሰፍን የሚሹ የአፍሪካ ሃገራት ከኢትዮጵያ ጎን መቆም እንዳለባቸው ተጠቆመ

አምባሳደር ነቢል ማህዲ

ኅዳር 11/2014 (ዋልታ) አሸባሪው ሕወሓትን በማስወገድ በአካባቢው ሰላም እንዲሰፍን የሚሹ የአፍሪካ ሃገራት ከኢትዮጵያ ጎን መቆም እንዳለባቸው በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ነቢል ማህዲ አሳሰቡ።

አንዳንድ ሃገራት አሸባሪውን ሕወሓት ከኢትዮጵያ መንግስት እኩል ለማስመሰል ከሚያደርጉት ሙከራ ሊቆጠቡ እንደሚገባም ጠይቀዋል።

አምባሳደር ነቢል እንደገለጹት አሸባሪው ሕወሓት ባለፈው ሰኔ ሰብአዊነትን ባስቀደመ ውሳኔ መከላከያ ከትግራይ ክልል መውጣቱን እንደመልካም አጋጣሚ በመወሰድ በአጎራባች የአፋርና የአማራ ክልሎች ላይ ወረራ በመፈጸም ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳቶችን እያደረሰ ነው።

በመሆኑ በአካባቢው ሰላም እንዲሰፍን የሚሹ የአፍሪካ ሃገራት ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆሙ ጠይቀዋል።

ቡድኑ በኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጀ በመሆኑ የድርጅቱን የጥፋት አድማስ ለማጥበብና አመራሮቹንም ለህግ ለማቅረብ የአፍሪካ ሃገራት ከኢትዮጵያ ጋር እንዲተባበሩም ጠይቀዋል።

“በዚህ ፈታኝ ወቅት የአፍሪካ አገሮች ከኢትዮጵያ ጋር በአንድነት መቆም አለባቸው፣ የአፍሪካ አገሮች በምዕራቡ ዓለም የሚዲያ ፕሮፖጋንዳ ግራ ሊጋቡ አይገባም” ብለዋል፡፡

በአፍሪካ ብቸኛዋ ነፃ አገር በሆነችው በኢትዮጵያ በኩል አፍሪካን አዲስ ቅኝ ግዛት ለመግዛት የምዕራባውያን አገሮች ድብቅ አጀንዳ አላቸው ሲሉም ከሰዋል።

ድብቅ አጀንዳቸው ኢትዮጵያን በማተራመስ ዳግመኛ ቀኝ ለመግዛት የሚያስችል እድል መፈለግ ነው ሲሉም ማስረዳታቸውን ሱዳን ፖስትን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል፡፡

አምባሳደሩ አሸባሪ ድርጅቱን በህዝብ ምርጫ ወደ ስልጣን ከመጣው ህጋዊ የኢትዮጵያ መንግስት ጋር እኩል ደረጃ ለማስቀመጥ የሚደረገው ሙከራ በፍጹም ተቀባይነት የለውም ብለዋል።

አሸባሪ ቡድኑ ዳግመኛ ወደ ስልጣኑ ቢመለስ የመጀመሪያዎቹ የአለመረጋጋትና ቀጣናዊ ምስቅልቅል ገፈት ቀማሾች የኢትዮጵያና አጎራባች ሃገራት በመሆናቸው ለኢትዮጵያ የሚያደርጉት ሁለንተናዊ እገዛ የሰላምና መረጋጋታቸው ዋስትና መሆኑንም አስምረውበታል።