ም/ጠ/ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አቻቸው ጋር ተወያዩ

ኅዳር 11/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዲሁም ከአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት ሰብሳቢ ክሪስቶፍ ሉቱንዱላ ጋር ተወያይተዋል፡፡

ውይይቱ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ግጭት እና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና የአፍሪካ ህብረት የመፍትሄው አካል በመሆን ሊጫወቱት የሚችለውን ሚና በተመለከተ ነው፡፡

የኢትዮጵያ አለመረጋጋት የአፍሪካ ህብረትን እና አህጉሩን እንደሚጎዳ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር እና የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ቴሽኬዲ ተናግረዋል፡፡

በዚህም በኢትዮጵያ ስልጣንን በኃይል ለመያዝ የሚደረግ ጥረትን እንደሚያወግዙ አስታወቀዋል፡፡

ሊቀመንበሩ ይህንን ያሉት በሀገራቸው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዲሁም በአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት ሰብሳቢ ክሪስቶፍ ሉቱንዱላ በኩል ነው፡፡

የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዝዳንት እና የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ፌሊክስ ቴሽኬዲ የኢትዮጵያን ሁኔታ በቅርበት ሲከታተሉ መቆየታቸውን ክሪስቶፍ ሉቱንዱላ ለአቶ ደመቀ ገልጸዋል።

በዚህም መሰረት ፕሬዝዳንት ትሺሴኬዲ አጋርነትንና ወንድማማችነትን ለማሳየት፣ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ሰላም መምጣት ያላቸውን ቁርጠኝነትን ለማሳየት ከፍተኛ የባለስልጣናት ልዑክ ወደ ኢትዮጵያ ልከዋል ተብሏል።

የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዝዳንት በኢትዮጵያ ውስጥ በኃይል ስልጣን ለመያዝ እና የግዛት አንድነትን እና የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ለማጋጨት የሚደረገውን ማንኛውንም ሙከራ በጽኑ እንደሚያወግዙ ገልጸዋል።

ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የኢትዮጵያ አለመረጋጋት የአፍሪካ ህብረትን እና አህጉሩን ይጎዳል ብላ እንደምታምንም የሀገሪቱ ባለስልጣን ገልጸዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የኮንጎ ፕሬዝዳንት በኢትዮጵያ የተጀመረውን የሰላም ጥረት ለመደገፍና ለማበረታታት ያደረጉትን ተነሳሽነት ማድነቃቸው ተገልጿል፡፡

በግጭቱ ውስጥ ባሉ ጉዳዮች ላይ ኢትዮጵያ ከሁለቱም ማለትም ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ከአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት ማየት የምትፈልጋቸውን ጉዳዮች ለኮንጎው ባለስልጣን ገልጸዋል ነው የተባለው፡፡

ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ሌሎች የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት የኢትዮጵያ መንግስት የአንድ ወገን የሰብአዊ መብት ተኩስ አቁም አዋጅ ቢያውጅም ህወሃት ይህንን ሃሳብ ውድቅ ማድረጉን እንዲገነዘቡም አቶ ደመቀ ጠይቀዋል፡፡

ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በአጎራባች ክልሎች ያለውን ግጭት እያሰፋና የኢትዮጵያን ሕዝብ ሰቆቃ እያራዘመ ያለውን ሕወሓትን እንድታወግዝ እንደሚጠብቁ ገልጸዋል፡፡