16ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ከአሁን በፊት ከነበረው በተለየ መልኩ እንደሚከበር ተገለጸ

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ዝሀራ ዑመር

ኅዳር 11/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ቀን ለ16ኛ ጊዜ “ወንድማማችነት ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት “በሚል መሪ ሀሳብ በድሬዳዋ ከተማ እንደሚከበር ተገልጿል፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ዛህራ ዑመድ በዘንድሮው ዓመት የሚከበረው  የብሔር ብሔረሰቦች ቀን አሸባሪው ሕወሓት በከፈተው ጦርነት ምክንያት መላው የኢትዮጵያ  ህዝብ የሀገርን ኅልውና ለመታደግ ያለውን ርብርብ በማጉላት አንድነታችንን የምናሳይበት ቀን በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

አሸባሪው የትሕነግ ቡድን በስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት በውሸት ትርክት የኢትዮጵያን ህዝብ ሲያታልል እንደነበር ገልፀው አሁን ላይም ስልጣንን ባለመጥገብ ተከብራ የኖረችን ሀገር ለሰላም  እጦት ዳርጓታል ብለዋል፡፡

ሀገርን ለማፈራረስ ኢትዮጵያ ጠል ከሆኑ ምዕራባውያን ጋር በመጣመር እየተንቀሳቀሰ የሚገኘውን የሽብር ቡድን ለመመከት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አንድነትን ማጠናከር እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የበዓሉ አስተባባሪ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ስንታየሁ ማሞ ቀኑ ከአሁን በፊት ከነበረው አከባበር በተለየ ለመከላከያ ሰራዊት ደም በመለገስ፣ የህዳሴ ግድቡን ከፍፃሜ ለማድረስ የህዳሴ ዋንጫ ርክክብ በማድረግ እንዲሁም በሀገር አቀፍ ሲምፖዚየም ላይ ትኩረት ያደረገ ይሆናል ብለዋል፡፡

በአመለወርቅ መኳንንት