ኢሳት በአፋር ክልል ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ አደረገ

ኅዳር 13/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት) በአፋር ክልል ለተፈናቀሉ ወገኖች የአይነት ድጋፍ አደረገ፡፡

የድርጅቱ ተወካይ ጋዜጠኛ መታሰቢያ ቀጸላ በክልሉ በአሸባሪው ሕወሓት ጥቃት የተፈናቀሉ ወገኖች የሚገኙበት ሁኔት አሳዛኝ መሆኑን ገልጻ የተፈናቀሉ ወገኞች ተጨማሪ ድጋፍን ያስፈልጋቸዋል ብላለች፡፡

የአፋር ሕዝብ የአሸባሪው ሕወሓት ኃይልን እስከወዲያኛው ለመደምሰስ በያዘው ቁርጠኛ አቋም ቡድኑ በክልሉ ንጹኃን ዜጎች እና ህጻናትን ገድሏል፤ ከቤት ንብረታቸው አፈናቅሏል ያለችው ጋዜጠኛ መታሰቢያ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ከአፋር ህዝብ ጎን ሊቆም እንደሚገባ ተናግራለች፡፡

በክልሉ 300ሺሕ ወገኖች የተፈናቀሉ መሆኑን የልሉ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች የገለጹ ሲሆን ለተፈናቃዮች የሚደረገው ድጋፍ በመንግሥት አቅም በቻ የሚሸፈን ባለመሆኑ ሌሎች ለጋሽ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል፡፡

በክልሉ የሽብር ቡድኑ ጥቃት የተፈናቃሉት አብዛኞቹ እናቶች እና ህጻናት በመሆናቸው አፋጣኝ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋልም ተብሏል፡፡

ዋልታ ያነጋገራቸው የተፈናቀሉ ወገኖችም የትሕነግ የሽብር ቡድን ንብረታቸውን እንዳወደመ እና እንስሳቶቻቸውን እንደ ገደለ ግልጸው በአሁን ሰዓት ከባድ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እየተደረገ ላለው ድጋፍ አመስግነው በዘላቂነት ወደ ቀያቸው የሚመለሱበት ሁኔታ እንዲመቻችም ጠይቀዋል፡፡
በሳራ ስዩም (ከአፋር)