ሻን ቴክስ ማኑፋክቸሪንግ ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ምርቱን ለውጪ ገበያ ላከ

ኅዳር 14/2014 (ዋልታ) በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የሚገኘው ሻን ቴክስ ማኑፋክቸሪንግ ኢትዮጵያ የተባለው አምራች ኩባንያ የመጀመሪያ ምርቶቹን ወደ ጣሊያን ሀገር መላኩ ተገለጸ፡፡

አምራች ኩባንያው በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ 10 ሄክታር በመውሰድ እና 65 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ፈሰስ በማድረግ ስራዎችን እየሰራ የቆየ ሲሆን አሁን ላይ ያመረታቸውን ከ45 ሺሕ በላይ የሹራብ ምርቶች ልኳል፡፡

በዚህም ከ80 ሺሕ የአሜሪካን ዶላር በላይ ከኤክስፖርት ማግኘት መቻሉ ነው የተገለጸው፡፡

ኩባንያው ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት የሚያመርት ሲሆን የምርቶቹን 90 በመቶ ለውጪ ገበያ እንዲሁም የቀረውን ደግሞ ለሀገር ውስጥ ገበያ ያቀርባል፡፡

ኩባንያው ለ500 ዜጎች የስራ እድል መፍጠሩን ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡