የጠ/ሚ/ር ዐቢይ ወደ ትግል ሜዳ መግባት ከፍተኛ ድል እያስገኘ መሆኑ ተገለጸ

ኅዳር 15/2014 (ዋልታ) የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ትግል ሜዳ ወርዶ የመምራት ውሳኔና የክተት ጥሪ በጦር ግንባር ከፍተኛ ድል እያስገኘ መሆኑን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ በወገን ጦርና ሕዝብ ላይ መነሳሳት እንደፈጠረም ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ በጦር ሜዳ የማታገል ውሳኔ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ መሪዎች አርዓያነት የሚመነጭ ነውም ብለዋል።

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ በወቅታዊ ጉዳዮች በሰጡት መግለጫ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባደረገው ሕዝበ ውሳኔ 11ኛው የአገሪቱ የፌደሬሽን አባል መሆኑን አረጋግጧል፤ በዚህም ክልሉ ትናንት ተመስርቷል ብለዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በዚህ ወቅት መመስረቱ አገሪቱ የምትከተለውን የእውነተኛ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ መሰረት ያፀና መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በመግለጫው ከኅልውና ዘመቻው ጎን ለጎን በምጣኔሃብትና ዲፕሎማሲ እንቅስቃሴው በርብርብ እንደሚሰራ ተመላክቷል፡፡

በአሸባሪው ኃይል በደረሰው ውድመትና ተፈጥሯዊ ድርቅ ሊደርስ የሚችለውን ችግር ለመታደግ ሀሉም መረባረብ እንደሚገባው መንግሥት ጥሪ አቅርቧል።