የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ግንባር መዝመት የኢትዮጵያውያንን የቆራጥነት ጥግ የሚያሳይ ነው – የመተሀራ ከተማ ነዋሪዎች

ኅዳር 16/2014 (ዋልታ) ከቀናት በፊት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአገር መከላከያ ሰራዊቱን ከፊት ቆሞ ለመምራት ወደ ግንባር መዝመታቸው ወትሮም ይሁን ዘንድሮ የኢትዮጵያዊያን ቆራጥነት ልኩ ምን ድረስ እንደሆነ የሚያሳይ መሆኑን የመተሀራ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከወራት በፊት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “ሀገሬን ከማስደፍር አንገቴ ቢቀላ መርጣለው” ብለው የገቡትን ቃል ኪዳን በተግባር እያሳዩ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

የሀገርን ዳር ድንበር ለማስከበርና የውስጥ ተላላኪ ኃይሎችን ለማጥፋት የሀገራችን መሪ ወደ ግንባር ዘምቶ ማንም ሰው ወደ ቤቱ ተመልሶ አይተኛም ያሉት ነዋሪዎቹ እኛም ከዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጎን ለመሰለፍ የምንሰስተው ህይወት የለንም ብለዋል።

ታሪክ አጋጣሚ ፈጥራልናለች የሚሉት የመተሀራ ነዋሪዎች የትላንቱን አድዋ በዚህ ትውልድ አድሰን የሀገራችንን ኅልውና በመጠበቅ እንደ ቀደምት ጀግኖች አባቶቻችን ዘመን የማይሽረውና ቀጣዩ ትውልድ አንገቱን ቀና አድርጎ በአለም አደባባይ የሚኮራበትን ዘላለማዊ ታሪክ ለመፃፍ እንታገላለን ሲሉም ገልጸዋል።

ንጋት ላይ የጀመረው የሽብርና የጥፋት ኃይሎቹን የሚቃወም እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን እና የአገር መከላከያ ሰራዊቱን የሚደግፍ ሰለፍ በመተሀራ እየተካሄደ ነው።

በታምራት ደሊል (ከመተሀራ)