የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን በቅጥር ግቢው ውስጥ ስለተፈጠረው ሁኔታ ማብራሪያ እንዲሰጥ ተጠየቀ

ኅዳር 16/2014 (ዋልታ) የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በተባበሩት መንግስታት አፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ቅጥር ግቢ ውስጥ ስለተፈጠረው ሁኔታ ኮሚሽኑን ማብራሪያ እንዲሰጠው ጠየቀ።

በኮሚሽኑ ቅጥር ግቢ ውስጥ በከተማዋ ረብሻ መፈጠሩንና የኮሚሽኑ ቅጥር ግቢ እንደታወከ በማስመሰል የተቀነባበረ የቪዲዮ ምስል ዛሬ ከማለዳው ጀምሮ የማህበራዊ ትስስር ገጾች መነጋገሪያ ሆኖ ውሏል፡፡

በጉዳዩ ላይ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጄላን አብዲ ሁኔታውን ኮሚሽናቸው እየተከታተለው መሆኑንና የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ የኢኮኖሚ ኮሚሽን ማብራሪያ እንዲሰጥ መጠየቁን ለአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ተናግረዋል፡፡

እንደአሜሪካ ኤምባሲ ያሉና ሚዛን የሳተ አቋም እያራመዱ ያሉ አንዳንድ ተቋማት በአዲስ አበባ የሽብር ጥቃት ሊፈፀም ይችላል በሚል የበሬ ወለደ የውሸት ወሬ ሰራተኞቻቸው ከተማዋን ለቀው እንዲወጡ እያስፈራሩ ይገኛሉ።

ዛሬ በድርጅቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ የተሰራው የሁከት ድራማም የዚህ የውሸት ፕሮፖጋንዳ መጠቀሚያ አንዱ አካል ሳይሆን እንዳልቀረ ብዙዎች እየገለጹ ይገኛሉ፡፡

የፌደራሉ መንግሥት የአሜሪካ ኤምባሲ ሽብር ፈጣሪ መግለጫዎችን ከማውጣት እንዲቆጠብ ሲያሳስብ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ የሚያሰጋ የሽብር ጥቃት የለም፤ ከፍተኛ ክትትልም እያደረግሁ ነው ብሏል።