የትምህርት ሚኒስትሩ በአገራችን ላለው ችግር መነሻው የትምህርት ስርዓቱ ደካማ በመሆኑ ነው አሉ

ኅዳር 17/2014 (ዋልታ) በአገራችን አሁን ያለው ችግር መነሻ የትምህርት ስርዓቱ ላይ ያለው ክፍተት መሆኑን የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ተናግረዋል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ከኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ መምህራንና አስተዳደር ሰራተኞች ጋር ውይይት አካሂደዋል፡፡

ውይይቱም የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ወደ ኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ እንዲያድግ በመንግስት መወሰኑን ተከትሎ ዩኒቨርሲቲን መልሶ በጠንካራ መሰረት ላይ ማደራጀት በሚቻልበትና እና ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ለማድርግ ያለመ ነው፡፡

አሁን በሀገሪቱ በተለያየ መንገድ የሚስተዋሉ ችግሮች ዋና መነሻው የትምህርት ስርዓቱ መውደቅ መሆኑን ሚኒስትሩ መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

በትምህርት ስርዓቱ ያለውን የትምህርት ጥራት መሰረታዊ ችግሮችን ከፖለቲካ አስተሳሰብ በማላቀቅና በጥልቀት በመረዳት ለመፍትሔው ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበትም ብለዋል፡፡

የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ብርሃነመስቀል ጠና (ዶ/ር)  ኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ከጅምሩ ጀምሮ አሁን እስከ ደረሰበት ድረስ የነበሩ ስኬቶችና ከአደረጃጀት አንፃር የነበሩ ከፍተኛ ተግዳሮቶችን ለትምህርት ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በመምህራን ሙያ ልማት ቀዳሚ ዩኒቨርሲቲ እንደነበርም ገልፀው በአዲስ መልክ የተቋቋመው በትምህርት ስርዓቱ ያሉ መሰረታዊ ችግሮችና ውድቀቶች ከስር መስረቱ በማጥናት ለመፍታት እንዲያስችል ነው ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው አሁን የተሰጠውን ተልዕኮ ሊመጥን የሚችል ራዕይና አደረጃጀት ቀርፆ ወደ ተግባር መግባት እንዳለበትም አቅጣጫ ተሰጥቷል፡፡