የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ግንባር መዝመት የኢትዮጵያውያንን ጀግንነት የሚያሳይ የአሸናፊነት ተምሳሌት ነው

ኅዳር 20/2014 (ዋልታ) የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ግንባር መዝመት የኢትዮጵያውያንን ጀግንነት የሚያሳይ የአሸናፊነት ተምሳሌት ነው ሲሉ የሸገር የብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት ሰራተኞች ገለፁ።

የድርጅቱ ሰራተኞች የውጭ ጣልቃ ገብነትን በመቃወም አንዳንድ ምዕራባውያን አገራ እጃቸውን ከኢትዮጵያ ላይ እንዲያነሱ ጠይቀዋል። የተቋሙ ሰራተኞች የ#በቃ #Nomore የሚል መርህ በማንገብ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

የሸገር ብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት ዋና ስራ አስኪያጅ ቢተው ደመላሽ በሉአላዊነት የማይደራደረው የኢትዮጵያ ህዝብ እንደ አያት ቅድመ አያቶቻችን ዛሬም ጠላትን ድባቅ መምታት ያውቅበታል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የድርጅቱ ሰራተኞችም ከወር ደመወዛቸው በመቀነስ ጀግናው የአገር መከላከያ ሰራዊትን በመደገፍ እንዲሁም ግንባር ድረስ በመዝመት እና የደም ልገሳ መርኃግብሮችን በማድረግ ደጀንነቱን እያሳየ ይገኛል ብለዋል።

ለአገር ሰላም እና እድገት ሁሉም የበኩሉን ማድረግ አለበት ያሉት የድርጅቱ ሰራተኞች የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ግንባር ድረስ መዝመት ወኔ ሆኖናል ብለዋል።

ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ሰራተኞች በዛሬው እለት ለ4ኛ ዙር የደም ልገሳ መርኃግብር አካሂደዋል።

በቁምነገር አሕመድ