ቻይና የአፍሪካ አገራትን መብትና ጥቅም ለማስከበር ቁርጠኛ ነኝ አለች

ኅዳር 20/2014 (ዋልታ) ቻይና የአፍሪካ አገራትን መብትና ጥቅም ለማስከበር ቁርጠኛ መሆኗን ገለጸች።

በአገር ውስጥ ጉዳዮች ላይ ጣልቃ መግባትን፣ ዘረኝነትን እና የአንድ ወገን ማዕቀቦችን አጥብቃ እንደምትቃወም የቻይኛ የውጭ ጉዳይ ረዳት ሚኒስትር እና ቃል አቀባይ ሁዋ ቹኒንግ ተናግረዋል።

በማደግ ላይ ያሉ አገራት ለሚሰጡት ፍትሓዊ ሐሳቦች ቆመን የጋራ ምኞታችንን እና ጥቅማችንን በተግባር መተርጎም አለብን ያሉት ሁዋ ቹኒንግ ቻይና በተለያዩ የልማት መርሃግብሮች ተግባራዊ በማድረግ ከአፍሪካ አገራት ጋር በቅርበት ትሰራለች ብለዋል።

ቻይና ለአፍሪካ ተጨማሪ አንድ ቢሊዮን ዶዝ ክትባት እንደምትለግስ እና 10 የህክምና ፕሮጀክቶችን በመተግበር 1 ሺሕ 500 የህክምና ባለሙያዎችን እንደምትልክም በቲውተር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት አመላክተዋል፡፡

በተጨማሪም የአፍሪካን የግብርና ዘርፍ ለማዘመን 500 የግብርና ባለሙያዎችን ወደ አኅጉሪቱ በመላክ ለዘመናዊ የአግሮቴክኖሎጂ ልውውጥ እና ስልጠና የጋራ ማዕከላትን እንደምታቋቋም ጠቁመዋል።

በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታትም ከአፍሪካ ወደ ቻይና የሚገባው የገቢ ንግድ ወደ 300 ቢሊዮን ዶላር ከፍ እንደሚል ገልጸው በአፍሪካ የወጪ ንግድን ለመደገፍ 10 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደምታደርግ አስታውቀዋል፡፡
በትዝታ መንግሥቱ