ወንጪ ሐይቅ ምርጥ የቱሪዝም መንደር ሆኖ ተመረጠ

ወንጪ ሐይቅ

ኅዳር 23/2014 (ዋልታ) በስፔን ማድሪድ እየተካሄደ በሚገኘው 24ኛው የዓለም የቱሪዝም ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ወንጪ ሐይቅ የ2021 ምርጥ የቱሪዝም መንደር ሆኖ ተመረጠ።

በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ የሚገኘው ወንጪ ሐይቅ ከ170 የቱሪዝም መንደሮች መካከል ቀዳሚ ሆኖ መመረጡ በጉባኤው ላይ ይፋ ተደርጓል።

የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ እንደተናገሩት ድንቅ የተፈጥሮ ሃብት ባለቤት የሆነው የወንጪ ሐይቅ ምርጥ የቱሪዝም መንደር ሆኖ የተመረጠው ባለው ዕምቅ የተፈጥሮ ሃብት ነው።

ወንጪ ሐይቅ ምርጥ የቱሪዝም መንደር ሆኖ በመመረጡ ‘እንኳን ደስ ያለን’ ያሉት ሚኒስትሯ የአካባቢውን የተፈጥሮ ጸጋ ተንከባክበው ለዚህ እንዲበቃ ላስቻሉት የአካባቢው ነዋሪዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

ለተፈጥሮ ሃብቱ እንዲህ ዓይነት ዓለም ዐቀፍ እውቅና መሰጠቱ ለሌሎችም አረዓያ የሚሆንና የበለጠ ለመስራት የሚያነሳሳ መሆኑን ጠቅሰዋል።

መንግስት ከፍተኛ ትኩረት ከሰጣቸው ዘርፎች መካከል አንዱ ቱሪዝም መሆኑን ገልጸው ማህበረሰብ ተኮር የሆነ ዘላቂ የቱሪዝም ልማት ስራዎች እንደሚሰሩ አመላክተዋል።

በተባበሩት መንግስታት ስር ያለው የአለም የቱሪዝም ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ዳዊት የተመራው የኢትዮጵያ ልዑክ በመድረኩ እየተሳተፈ እንደሚገኝ የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።