ሰበር ዜና ድሉ በመሐል ሀገር እንደሚደገም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ገለፁ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

ኅዳር 23/2014 (ዋልታ) በምሥራቅና በምዕራብ የተገኘው ድል በመሐል ሀገር እንደሚደገም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለፁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት በሦስተኛው ቁልፍ ግንባር ተገኝተው ከሰራዊቱ ጋር በመከሩበት ጊዜ ነው።

ከሰሞኑ በሚሠሩ ኦፕሬሽኖች በወራሪውና አሸባሪው ሕወሓት የተያዙ ተጨማሪ ከተሞች ነጻ እንደሚወጡ የገለፁ ሲሆን ለወረራ የገባው አሸባሪ ምንም ነገር ይዞ እንዳይወጣ ሕዝቡ ተደራጅቶ ማስቀረት እንዳለበት ጥሪ አድርገዋል።

ጠላት ፈርሷል፤ ተበትኗል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሁን ጠላት ያለው አማራጭ የሰረቀውን አስረክቦ እጁን መስጠት ነው ብለዋል። የሰረቀውን አስረክቦ እጁን ከሰጠ ምርኮኞችን ተከባክቦ መያዝ የጀግና ባህላችን ነውም ሲሉ አክለዋል፡፡

ከአሸባሪው ሕወሓት ነፃ በወጡ አካባቢዎች በአስቸኳይ መስተዳድሩን በቶሎ መልሶ ማቋቋም እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሳስበዋል።

ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነዋል፤ ወታደሩ በከፍተኛ ሞራል ላይ ነው ሲሉም የወገን ኃይል ያለበትን ገልፀዋል፡፡

ሕዝቡ እስካሁን ላደረገው ተሳትፎ ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን አንድነታችን የተጠበቀ ይሁን፤ የአሉባልታ ወሬ ወጀብ አይውሰደን፤ አንድ ሆነን የማትደፈር ሀገር ለልጆቻችን እናስረክብ ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መልእክት አስተላልፈዋል።