ሁሉም ኢትዮጵያዊ ባንዳዎችን እቅሙ በፈቀደው ሁሉ ያለምህረት ሊፋለማቸው ይገባል –  የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር

ተመስገን ጥሩነህ

ኅዳር 24/2014 (ዋልታ) ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሰፈር እና ሀገር ባንዳዎችን እቅሙ በፈቀደው ሁሉ ያለምህረት ሊፋለማቸው እንደሚገባ የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ተመስገን ጥሩነህ ጥሪ አቀረቡ፡፡

ዳይሬክተሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው በፃፉት መልዕክት “እነሱ እኩይ ዓላማ ይዘው ለመዝረፍ፣ ንፁሃንን ለመግደል፣ ሰራዊታችንን ለመበተን እና ሀገር ለማፍረስ ይዋጉናል ፤ እኛ ደግሞ ለፍትህ፣ ለነፃነታችን፣ ለክብራችን፣ ሀገራችንን ለመጠበቅ እንፋለማቸዋለን” ብለዋል፡፡

“የሽብር ቡድኑ ሞት ዓላማ ቢስ ከንቱ መስዋዕትነት ሲሆን የእኛ ደግሞ የሀገርን እና የህዝብን የቆዬ የአይደፈሬነት ክብር አስጠብቆ ለትውልድ ለማስተላለፍ የሚከፈል ዘመን ተሻጋሪ እና ታሪካዊ ክቡር መስዋዕትነት ነው” ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በመሆኑም ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሰፈር እና ሀገር ባንዳዎችን እቅሙ በፈቀደው ሁሉ ያለምህረት ሊፋለማቸው እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል፡፡