ዓለም ዐቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን እየተከበረ ነው

ኅዳር 24/2014 (ዋልታ) ዓለም ዐቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን በኢትዮጵያ ለ29ኛ ጊዜ፤ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ለ30ኛ ጊዜ እየተከበረ ይገኛል፡፡
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ቀኑን አስመልክተው በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት አለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን “የአካል ጉዳተኞችን መሪነትና ተሳትፎን በማረጋገጥ አካታች፣ ተደራሽና ዘላቂ ድኅረ ኮቪድ-19 ዓለም እንገንባ’ በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ እየተከበረ ይገኛል ብለዋል።
ሚኒስትሯ የአካል ጉዳተኞችን ፍትሃዊና ጥራት ያለው አገልግሎት ተጠቃሚነት ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር በጋራ መስራት አለብን ሲሉም ጠይቀዋል።
በኢትዮጵያ ለ29ኛ ጊዜ የሚከበረው የአካል ጉዳተኞች ቀን በርካታ እንግዶች በተገኙበት በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ እየተከበረ ይገኛል፡፡
በተጨማሪም የሶማሌ ክልል ርዕስ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሃመድ፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬን (ዶ/ር) እንዲሁም ከፍተኛ የፌዴራልና የክልል የሥራ ኃላፊዎች በክልሉ የሚገኘውን የአካል ጉዳተኞች ማዕከል የአገልግሎት አሰጣጥ እና ያለበትን ደረጃ ጎብኝተዋል።