ከ72 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመቱ የኮንትሮባንድ እቃዎች ተያዙ

የኮንትሮባንድ እቃዎች

ኅዳር 25/2014 (ዋልታ) ባሳለፍነው ሳምንት ከ72 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የገቢና የወጭ የኮንትሮባንድ እቃዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ፡፡

የጉምሩክ ኮሚሽን በሳምንቱ ውስጥ በተደረገ ክትትል 47 ነጥብ 4 ብር በላይ የገቢ ኮንትሮባንድ እቃዎች እና 24 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር የሚያወጡ የወጭ ኮንትሮባንድ እቃዎች በተለያዩ  ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች መያዛቸውን አስታውቋል፡፡

የገቢ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዙት ሞያሌ፣ አዳማ እና ሐዋሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ሲሆኑ በቅደም ተከተል 15 ነጥብ 4 ሚሊየን፣ 12 ሚሊየን እና 5 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎችን መያዝ ችለዋል፡፡

የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ የተያዙት የጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኞች፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የክልል ፖሊስ አባላትና ኅብረተሰቡ በጋራ ባደረጉት ጥረት ሲሆን የኮንትባንድ ዕቃዎቹን ሲያዘዋውሩ የተገኙ ሁለት ተጠርጣሪዎችም በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡

በቁጥጥር ስር ከዋሉት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል ወርቅ፣ የተለያዩ አልባሳት፣ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች፣ ቡና፣ መድሀኒት፣ የመዋቢያ እቃዎች የጦር መሳሪያዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ እጾች እና የተለያዩ ሀገራት ገንዘቦች ይገኙበታል፡፡

የኮንትሮባንድ እና ህገወጥ ንግድ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽእኖ ለመከላከል የጉምሩክ ኮሚሽን ብቻ የሚያደርገው እንቅስቃሴ በቂ ባለመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላትና ኅብረተሰቡ የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ ማቅረቡን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡