የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ የዘማች ቤተሰቦችን ሰብል ሰበሰቡ

ኅዳር 25/2014 (ዋልታ) የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ መምህራንና ሠራተኞች የክተት ጥሪ ዘማች ቤተሰቦችን ሰብል ሰብስበዋል።
በተከናወነው የዘማች ቤተሰብ ሰብል የመሰብሰብ መርኃ ግብር ላይ የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዷለም ተሳትፈዋል።
ሚኒስትሩ የዩኒቨርሲቲው መምህራን እና ሠራተኞች የተቀናጀ ሥራን አድንቀው ትብብሩ በሌሎች አገራዊ ጥሪዎች ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።
የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንት ክንዴ ገበየሁ (ዶ/ር) ለሁለት ሳምንት በተካሄደው የዘማች ቤተሰብ ሰብል የመሰብሰብ ዘመቻ መምህራን እና ሠራተኞች ስኬታማ ሥራዎችን እንደፈጸሙ ተናግረዋል።
በሊቦ-ከምከም፣ ፎገራ፣ ደራ እና ጉና በጌምድር ወረዳዎች 142 ሄክታር የሩዝ፣ የዳጉሳ እና የባቄላ ሰብሎች ለክተት ጥሪ ዘማች ቤተሰብ፣ ለአቅመ ደካሞች እና በመስኖ ገብ ቀጣናዎች መሰብሰብ መቻሉን መግለፃቸውን ከዩኒቨርሲቲው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።