መንግሥት የትግራይ ሕዝብ አሸባሪው ትሕነግን ልጆቻችን የት ገቡ ሲል እየጠየቀ ነው አለ

ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)

ኅዳር 30/2014 (ዋልታ) አሸባሪው ትሕነግ በአሁኑ ሰዓት የትግራይን ሕዝብ አስገድዶ በመሰብሰብ የተለመደ የውሸት ፕሮፖጋንዳ ሊነዛ ቢሞክርም የትግራይ ሕዝብ ግን ልጆቻችን የት ገቡ በማለት በመጠየቅ ላይ መሆኑን መንግስት ገለጸ፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ዛሬ በሰጡት መግለጫ በሳለፍነው ሳምንት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሲመራ የነበረው ዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት ከፍተኛ ድል የተገኘበት እና ኢትዮጵያውያን አሸናፊነታቸውን ያረጋገጡበት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ዘመቻው የኅብረ ብሔራዊ አንድነት የታየበት እና ኢትዮጵያውያን በአንድ ላይ የቆሙበት መሆኑን አመላክተዋል፡፡

በተመሳሳይም በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር ሙሉ በሙሉ ነፃ የወጣ ሲሆን በቀጣይም አሸባሪው ሕወሓት በወረራ የያዛቸው ቦታዎች በቅርቡ ነፃ ይወጣሉ ብለዋል::

ወራሪው ኃይል በኮምቦልቻ፣ አንፆኪያ፣ ገምዛ እና በሌሎችም በወረራ በያዛቸው ቦታዎች ዘግናኝ ጭፍጨፋ ማካሄዱ እና የጅምላ መቃብር መገኘቱም ተመላክቷል::

ይህም አሸባሪው የትሕነግ ኃይል በወረራ በያዛቸው ቦታዎች ሁሉ የዘር ማጥፋት ወንጀል መፈጸሙን ይመላክታል ብለዋል::

በምዕራብ ኦሮሚያ፣ በጉጂ፣ በቦረና እና በሌሎችም የክልሉ አካባቢዎች የትሕነግ ተላላኪ የሆነው አሸባሪ ሸኔ ታጣቂዎች በፀጥታ ኃይሎች መደምሰሱንም አመልክተዋል።

በሌላ በኩል በነገው እለት የሰብዓዊ መብት ቀን የሚከበር ሲሆን አሸባሪው የትሕነግ ቡድን በንፁሀን ዜጎች ላይ ያደረሰውን ዘግናኝ ጭፍጨፋ በማውገዝ እና ተጎጂዎችን በማሰብ እንደሚካሄድ ሚኒስትሩ ገልጸዋል::

በሜሮን መስፍን