ኩባ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማሳደግ ቁርጠኛ መሆኗን ገለጸች

ኅዳር 30/2014 (ዋልታ) በኢትዮጵያ የኩባ አምባሳደር ጆርግ ኤፍ.ኤል ኒኮላስ ኩባ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማሳደግ ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ አዲስ የተሾሙት የኩባ አምባሳደር ጆርግ ኤፍ.ኤል ኒኮላስ የሹመት ደብዳቤያቸውን ቅጂ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኘሮቶኮል ጉዳዮች ምክትል ሹም አምባሳደር አለማየሁ ሰዋአገኝ አቅርበዋል።

በአሁኑ ወቅት አንዳንድ ሀገራት በኢትዮጵያ ላይ የተቀናጀ ጫና እና የሃሰተኛ የሚድያ ዘመቻ እያካሄዱባት እንደሚገኝ ያነሱት አምባሳደሩ የኩባ መንግስት ይህን ድርጊት እንደሚያወግዝ ጠቅሰዋል።

እንደ ቀድሞ ሁሉ ኩባ ከኢትዮጵያ ጎን መሆኗን ገልጸው አስፈላጊውን ዲኘሎማሲያዊ ድጋፍ እንደምትሰጥ አረጋግጠዋል።

አዲስ የተሸሙት አምባሳደሩ በሥራ ቆይታቸው በትምህርት፣ ህክምና እና የስኳር ልማት መስክ ያለውን የሁለቱን ሃገራት ትበብር ለማሳደግ እንደሚሰሩ ገልፀዋል።

አምባሳደር አለማየሁ ሰዋአገኝ በበኩላቸው ኩባውያን ለኢትዮጵያ ሉአላዊነት መከበር ታላቅ መስዋትነት መክፈላቸውን በማስታወስ ሀገራቱ ህዝቦቻቸውን ይበልጥ ተጠቃሚ በሚያደርጉ መስኮች ላይ አተኩረው ግንኙነታቸውን ማጠናከር እንደሚገባቸው ማንሳታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃልአቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡