ኮሚሸኑ ተመላላሽ ህገ ወጥ ነጋዴዎችን አስጠነቀቀ

ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ

ታኅሣሥ 1/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሸን ተመላላሽ ህገ ወጥ ነጋዴዎችን አስጠነቅቋል፡፡

የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በመመሪያ 51/2010 መሰረት መንገደኞች በየብስ እና በአውሮፕላን የግል እቃ መገልገያ ይዘው መግባት የሚችሉ መሆኑን አስታውቀዋል።

መመሪያው ጤናማ እና ህጋዊ እንቅስቃሴን እንደማያግድ የገለጹት ኮሚሽነሩ በአንፃሩ ደግሞ የንግድ ፍቃድ የሌላቸው እና የሀገር ውስጥ ታክስ እና ቀረጥ የማይከፍሉትን አካለት ኮሚሽኑ እያገደ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

የመንግስት ሰራተኞች፣ የአየር መንገድ ሰራተኞች፣ ሆስተሶች እና ሌሎችም በህገ ወጥ ንግድ ላይ የተሰማሩ አካለት ሙሉ መረጃ ኮሚሽኑ ያለው መሆኑንም ገልፀዋል።

ከሰሞኑ የተፈጠረው ውዥንብርም በህገወጥ ነጋዴዎች ላይ ኮሚሽኑ እያደረገ ካለው ጥብቅ ቁጥጥር ጋር ተያይዞ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል ህጋዊ የሆኑ እና ፍቃድ ያላቸው መንገደኞች ትክክለኛ አገልግሎት ተጓድሏል የሚሉ አካላት ካሉ በህጋዊ መጠየቂያ መንገድ ኮሚሽኑን መጠየቅ ይችላሉም ተብሏል።

ነገር ግን የኮሚሽኑን አሰራር በተመለከተ በየሶሻል ሚዲያው የሀሰት መረጃ የሚያሰራጩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ጉምሩክ ኮሚሽን አስጠንቅቋል።

የመንግስትን ጥሪ ተከትሎ ለገና በዓል ወደ ሀገር የሚገቡ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዳይንገላቱ በከፍተኛ የአገልግሎት ጥራት የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ሊያገለግላቸው መዘጋጀቱንም አስታውቋል።

ለቤተሰባቸው፣ ለወዳጅ ዘመድ እንዲሁም ለተፈናቀሉ ወገኖች እቃ ይዘው ሲገቡም በከፍተኛ ጥራት ይስተናገዳሉ ተብሏል።

በሜሮን መስፍን