የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች የናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ የግንባታ እንቅስቃሴን ጎበኙ

የማዕድን ሚኒስትር ታከለ ኡማ

ታኅሣሥ 2/2014 (ዋልታ) በሰሜን ሸዋ በቻይና ባለሃብቶችና በኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ባለቤትነት እየተገነባ የሚገኘውን የናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ የግንባታ እንቅስቃሴ በመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተጎብኝቷል።

በጉብኝቱ ላይ የማዕድን ሚኒስትር ታከለ ኡማን ጨምሮ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) እና ከፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ተገኝተዋል።

በሁሉም ዘርፍ ሀገራዊ የምርት አቅማችንን በማሳደግ በሀገራዊ ፍላጎትና አቅርቦት መካከል መመጣጠን መፍጠር ዋነኛው አላማችን ነው ያሉት የማዕድን ሚኒስትር ታከለ ኡማ ይህንን በማሳካት በየትኛውም አካባቢ የሚገኝ የማዕድን ሃብታችንን ጥቅም ላይ እንዲውል እናደርጋለን ብለዋል።

ይህም በአንድ በኩል በምርት ላይ ያሉ አምራች ፋብሪካዎችን በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ በማገዝ በሌላ በኩል ደግሞ አቅምና የሥራ ፍላጎት ያላቸውን አምራች ኢንዱስትሪዎችን በስፋት ወደ ኢንቨስትመንት በማስገባት የሚሳካ ይሆናል ነው ያሉት።

የግንባታ እንቅስቃሴው ተጠናቆ በአፋጣኝ ወደ ምርት እንዲገባም ተገቢውን ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ከአማራ ክልል ጋር በትብብር ይሰራል ብለዋል፡፡

ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት በክልሉ ያለውን የማዕድን ምርት በአፋጣኝ ወደ እንቅስቃሴ መመለስም በፍጥነትና በከፍተኛ ትኩረት የሚሰራ ቀጣይ ተግባር ነው ብለዋል።