መንግሥት አሸባሪው ሕወሓት የሕዝብ ቁጥር 1 ጠላትነቱን አስመስክሯል አለ

ታኅሣሥ 2/2014 (ዋልታ) አሸባሪው ሕወሓት የሕዝብ ቁጥር 1 ጠላት መሆኑን በሚገባ አስመስክሯል ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኔስቴር አስታወቀ፡፡

የሽብር ቡድኑ በአማራ ክልል በወረራቸው ቦታዎች ሁሉ ያወደማቸውን ተቋማት በመጥቀስ የግፉን ጥግ ለዓለም ያሳወቀው ሚኒስቴሩ ቡድኑ የሕዝብ ቁጥር 1 ጠላት መሆኑን እንዳስመሰከረ አጽንኦት ሰጥቷል፡፡

ሚኒስቴሩ በቲውተር ገጹ ባጋራቸው መረጃዎች ቡድኑ ካወደማቸው ተቋማት ጥቂቱን ለአብነት ሲል አቅርቧል፡፡

አሸባሪው ሕወሓት በአማራ ክልል የጤና ተቋማትን፣ የሕዝብ አውቶቡሶችን፣ ሆቴሎችን፣ አየር ማረፊያ (ኤርፖርቶችን)ና ባንኮችን ማውደሙን አሳውቋል፡፡

ሚኒስቴሩ እንዲህ ዓይነቱን ውድመት ማድረስ የሽብር ቡድኑ በፕሮፖጋንዳው ከሚያስተጋባውና ከሚያጭበረብርበት ‹ትግራይን መጠበቅ (መከላከል)› ከሚል ስሁት ትርክት ጋር ምንስ ያገናኘዋል ሲል ጥያቄን አቅርቧል፡፡

የሽብር ቡድኑን በዘገባዎቻቸው ሲያሞጋግሱ የሚውሉ፣ የዴሞክራሲና ሰብኣዊነት ብቸኛ አስተማሪዎች እኛ ነን ሲሉ የሚታበዩ የውጭ መገናኛ ብዙኃንና መንግሥታት እንዲሁም ዓለም ዐቀፍ ተቋማት ቡድኑ የፈፀማቸው የጅምላ ግድያዎች እና ያወደማቸው የሕዝብ ተቋማት መገለፅ ሲጀምሩ ግን ድምፃቸውን አጥፍተዋል፡፡