የአማራ ወጣቶች መከላከያ ሰራዊትን እንዲቀላቀሉ ጥሪ ቀረበ

ታኅሣሥ 3/2014 (ዋልታ) የአማራ ወጣቶች የአገር መከላከያ ሰራዊትን በስፋት እንዲቀላቀሉ ጥሪ ቀረበ።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ገዱ አንዳርጋቸውና ከፍተኛ ኃላፊዎች ከባሕር ዳር ከተማ ወጣቶች ጋር በወቅታዊና አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በባሕር ዳር ውይይት አድርገዋል።
በውይይት መድረኩ የመተከል ዞን የተቀናጀ ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ሌተናል ጄነራል ሀሰን ኢብራሂምና የባሕር ዳር ከተማ ከንቲባ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) ተገኝተዋል።
የመተከል ዞን የተቀናጀ ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ሌተናል ጄነራል ሀሰን ኢብራሂም አሸባሪው ሕወሓት በአማራ ላይ እያደረሰ ያለውን ግፍ ለማስቆምና አሸባሪ ቡድኑን እስከመጨረሻው ለማጥፋትም ሆነ የውስጥና የውጭ የኢትዮጵያ ጠላቶችን በመመከት በዘላቂነት ሕዝብን ከስጋት ነፃ ለማድረግ ወጣቶች መከላከያን በስፋት እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ገዱ በበኩላቸው በተለይ በዚህ ወቅት የአማራ ወጣት ያለምንም ልዩነት አንድ ሆኖ አሸባሪውን ሕወሓት በመደምሰስ ሕዝቡን ከወረራ ነፃ ለማውጣት በንቃት እንዲረባረብ ጠይቀዋል።
እንደኢብኮ ዘገባ በአገር መከላከያ ሰራዊት በመታቀፍና በአግባቡ በመሰልጠን ሕዝብን በዘላቂነት ማስከበር እንደሚገባም አፅንኦት ሰጥተዋል።