የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሪታሪያት ቢልለኔ ስዩም የአሜሪካን መግለጫ ተቹ

ታኅሣሥ 5/2014 (ዋልታ) አሜሪካ አሸባሪው ሕወሓት በአማራና በአፋር ክልሎች የተፈፀሙ ወንጀሎች አሳስቦኛል ስትል ባወጣችው መግለጫ ላይ ‘ያልተረጋገጡ ሪፖርቶች’ የሚል ሐሳብ ማንሳቷን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሪታሪያት ቢልለኔ ስዩም ተቹ።
ፕሬስ ሴክሪታሪዋ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልእክት አሜሪካ የምትደግፈው አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በኃይል በያዛቸው የአማራና አፋር አካባቢዎች በንጹሃን ዜጎች ላይ ወንጀል ሲፈጽም “ያልተረጋገጠ ሪፖርቶች” ነው ማለት ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም ብለዋል፡፡
አሸባሪ ቡድኑ በተቀነባበረ መንገድ ሲያለቅስ እንደ እውነት ይቆጠራል በማለትም ኢትዮጵያ ከአሸባሪ ቡድን እኩል መታየቷ አግባብ ባለመሆኑ “በቃ” ትላለች ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
አሜሪካ በአሸባሪው ሕወሓት የደረሱ የሰብኣዊ መብት ጥሰቶች፣ የጅምላ ጭፍጨፋዎች እና የመሰረተ ልማት ውድመቶችን በዝምታ ማለፍን በመምረጥ ወንጀሉን ሁሉ የኢትዮጵያ መንግሥት ላይ መለጠፍን መርጣለች፡፡
ከሰሞኑ በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቷ የቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት በኩል ባወጣችው መግለጫ ቡድኑ ያደረሰው ጥፋት እንዳሳሰባት በገለፀችበት መስመር መልሳ ያልተረጋገጡ ሪፖርቶች ስትልም የንፁሃን በጅምላ መገደል ቸል ብላ የፖለቲካ ፍላጎቷን ሚዛን ለማስጠበቅ ስትሞክር ታይቷል።