አምባሳደር ፍፁም አረጋ በእርዳታ ጫኝ ተሽከርካሪዎች ጉዳይ የዓለም ዐቀፉን ማኅበረሰብ ዝምታ ኮነኑ

ታኅሣሥ 6/2014 (ዋልታ) ሰብኣዊ እርዳታ ጭነው ወደ ትግራይ ክልል የሄዱ ከ1 ሺሕ በላይ ተሽከርካሪዎች አለመመለሳቸውን አስመልክቶ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ የዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ ዝምታን ኮነኑ፡፡
እንደ አምባሳደር ፍጹም ገለጻ ባለፈው ወር መጨረሻ እርዳታ ጭነው ወደ ትግራይ የሄዱትን 203 ተሸከርካሪዎች ጨምሮ እስካሁን ከ1 ሺሕ በላይ ተሽከርካሪዎች አልተመለሱም፡፡
እነዚህ ተሸከርካሪዎች እርዳታውን አድርሰው መመለስ ሲገባቸው ለአሸባሪው የሕወሓት ታጣቂዎች የትራንስፖርት አገልግሎትና የተዘረፈ ንብረት ማመላለሻ እየዋሉ መሆኑን አስታውሰዋል።
በሆነው ባልሆነው ኢትዮጵያን ሲወነጅሉ ውለው የሚያድሩት አንዳንድ ዓለም ዐቀፍ ተቋማትና አገራት ይህን እኩይ ተግባር አለመኮነናቸው የኢትዮጵያን እውነት ለመስማት እንደተሳናቸው አመላካች ነውም ብለዋል፡፡