የተለያዩ ተቋማት ለአፋር ክልል ከ5 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ

ታኅሣሥ 7/2014 (ዋልታ) የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ ኢትዮ-ቴሌኮምና አዲስ አበባ ፖሊስ በአፋር ክልል በአሸባሪው ሕወሓት ወራሪ ውድመት ለደረሰባቸው ፖሊስ ጣቢያዎች ሥራ ማስጀመር የሚያስችል ከ5 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል።
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል አሸባሪው ሕወሓት ወረራ በፈፀመባቸው የአፋርና አማራ ክልሎች በርካታ መሰረተ ልማት ማውደሙን አንስተው በአፋር ክልል ስምንት የፖሊስ ጣቢያዎች መውደማቸውን ተናግረዋል።
የአፋር ሕዝብ ከጀግናው የአገር መከላከያ ሰራዊት ጋር በመሆን ኢትዮጵያን ከወራሪው ኃይል ለመታደግ ያደረጉት የጀግንነት ተጋድሎ ትውልድ የማይረሳው ነው ያሉት ኮሚሽነር ጀነራሉ አገርን ለመበታተንና ለማተራመስ ቆርጠው የተነሱትን ወንጀለኞች ለህግ በማቅረብ የሕዝብ ሰላም እንዲመለስ የማድረግ ሥራ ይሰራል ብለዋል።
የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ በጦርነቱ የተጎዳውን የቴሌኮም መሰረተ ልማት ለመጠገን ሰራተኞችን ማሰማራታቸውንና አገልግሎቱን እያስጀመሩ መሆናቸውን ገልጸው ለተፈናቀሉ ወገኖች የምናደርገው ድጋፍ ይቀጥላል ነው ያሉት።
የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ኢትዮጵያን የጦርነት አውድማ ለማድረግ ያሰበውን ጠላት በኅብረት መመከት እንደተቻለ ገልጸው በዚህም የፌዴራል ፖሊስና ኢትዮ-ቴሌኮም ድርሻ ትልቅ መሆኑን አመልክተዋል።
የአሸባሪው ቡድን እየተቀበረ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ባጠረ ጊዜ ውስጥ ሀገርን ወደ ሰላምና ልማት የመመለስ ሥራ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
ከውጭና ከውስጥ የሚመጣን ጠላት ኢትዮጵያዊያን አንድነታቸውን አጠናክረው ሊመክቱ እንደሚገባም ተመልክቷል።
በሳራ ስዩም (ከግንባር)