የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራር ክህሎትን ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ ተገለጸ

ታኅሣሥ 9/2014 (ዋልታ) የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጥራት ያለው ትምህርትን ተደራሽ ከማድረግ ጎን ለጎን የአመራር ክህሎትን በማሳደግ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ተገለጸ።

በከፍተኛ ትምህርት ተቋሟት ውስጥ የሚስተዋለውን የአመራር እንከኖችን ለመቅረፍ የአመራር ስልጠና ሲሰጥ መቆየቱም ነው የተገለጸው።

የቀድሞ ሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር እንዲሁም በጀርመን መንግስት በተደረገ ድጋፍ ላለፉት ሶስት ዓመታት ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ስልጠና ስሰጥ የቆዬ ሲሆን ስልጠናቸውን በብቃት ያጠናቀቁ 377 ሰልጣኞች በመካከለኛ አመራር ዘርፍ ተመርቀዋል። ከነዚህም ውስጥ 161 ሴቶች ሲሆኑ 216 ወንዶች መሆናቸው ተመላክቷል።

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ 7 ነጥብ 7 በመቶ የነበረውን የሴት አመራር ተሳትፎ በአሁኑ ወቅት 42 ነጥብ 7 በመቶ ማድረስ መቻሉም ተገልጿል።

ኢትዮጵያ ከጠቅላላ በጀት 19 በመቶ የሚሆነውን ለከፍተኛ ትምህርት ተቋሟት በመመደብ በዓለማችን ካሉ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ልቀት ከሚተጉ ሀገራት ግምባር ቀደም መሆኗም ተመላክቷል።

በኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት 55 የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተልዕኳቸውን እየፈፀሙ ይገኛሉም ነው የተባለው።

በሃኒ አበበ