አሸባሪው ሕወሓት “በመንግሥት የተፈጸመ ጅምላ ጭፍጨፋ” ለሚል የሀሰት ፕሮፖጋንዳ እየተዘጋጀ ነው

ታኅሣሥ 12/2014 (ዋልታ) በኢትዮጵያ ጥምር ጦር የተቀናጀ ጥቃት ሽንፈት ተከናንቦ ወደ ትግራይ የሸሸው ወራሪው የሕወሓት ኃይል በየአውደ ውጊያው ከሞቱና ከቆሰሉ ታጣቂዎቹ የተወሰኑትን ወደ ትግራይ ይዞ በመሸሽ ላይ መሆኑን የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን መረጃ ምንጮች ተናግረዋል፡፡

ቡድኑ  ወቅታዊ ሁኔታን አስመልክቶ በምስጢር ባደረገው ስብሰባ የኢትዮጵያ ጥምር ጦር አሁን ባለው ቁመናና ግስጋሴ ወደ መቀሌ በአጭር ጊዜ ሊገባ ይችላል የሚለውን መላምት  ሊያጋጥሙት ከሚችሉት ችግሮች እንደ አንዱ አድርጎ የገመገመ ሲሆን ይህ ከተከሰተ በሚልም ዓለም ዐቀፉን ማኅበረሠብና የትግራይን ሕዝብ የሚያጭበረብርበት የሴራ እቅድ ማዘጋጀቱ ታውቋል፡፡

እንደ መረጃ ምንጮች ወራሪው የሕወሓት ኃይል ባዘጋጀው እቅድ መሰረት በየአውደ ውጊያው ከሞቱና ከቆሰሉ ታጣቂዎቹ የተወሰኑትን ወደ ትግራይ ይዞ በመሸሽ የመከላከያ ሠራዊት ወደ ትግራይ ከገባ “የመንግሥት ኃይል ጅምላ ጭፍጨፋ ወይም የዘር ማጥፋት እየፈጸመ ነው” በማለት በሙትና ቁስለኛ  ታጣቂዎቹ ምስል ለመነገድ አስቧል፡፡

እየተቀነባበረ ያለው ሴራ ሰሞኑን የመንግስታቱ ሰብኣዊ መብቶች ምክር ቤት  ልዩ ስብሰባ አድርጎ ካሳለፈው ውሳኔ ጋር ተመጋጋቢ መሆኑን የጠቆሙት ምንጮች ምክር ቤቱ  ከዚህ ቀደም ከኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር በመሆን ምርመራ አድርጎ ሪፖርት የቀረበበትን ጉዳይ እንደ አዲስ እንዲታይ በምዕራባውያን ዘዋሪነት ያሳለፈው ውሳኔ ለዚህ ሴራ አጋዥ እንዲሆን ታቅዷል የሚል ጥርጣሬ ማሳደሩን ገልጸዋል፡፡

የመከላከያ ሠራዊት ወደ ትግራይ ቢገባ ቡድኑ ከየግንባሩ የሰበሰባቸውን ሙትና ቁስለኛ ታጣቂዎቹን ምስል በማሰራጨት የተባበሩት መንግሥታት ሰብኣዊ መብቶች ምክር ቤት የሰሞኑ ውሳኔ ምክንያታዊ ነው የሚል ተቀባይነት እንዲያገኝ ለምእራባውያን ታዛዥ ከሆኑ የተለያዩ ዓለም ዐቀፍ የሰብኣዊ መብት ድርጅቶችና መገናኛ ብዙኃን ጋር ተናቦ ለመስራት የታቀደ መሆኑን የገለጹት የፋና ምንጮች የመንግሥታቱ ውሳኔ የሀገር ሉዓላዊነት የሚጋፋና ፖለቲካዊ አንድምታ ያለው ነው በሚል ከ22 ሀገራት ተቃውሞ እንደገጠመው አስታውሰዋል፡፡