የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በአማራ ክልል ለተፈናቀሉ ዜጎች የ15 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ

ታኅሣሥ 13/2014 (ዋልታ) የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በአሸባሪው ሕወሓት በአማራ ክልል ለተፈናቀሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚውል የ15 ሚሊዮን ብር የገንዘብ እና የዓይነት ድጋፍ አደረገ።

ድጋፉን በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጀዋር የተመራው የከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የአገር ሽማግሌዎች ለአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) አስረክበዋል።

ከንቲባው በርክክቡ ወቅት አማራ ክልል ሀገር ላይ የተጠነሰሰውን ሴራ ከመከላከያ ጋር በመቀናጀት በመመከት ለከፈለው ዋጋ ምስጋና አቅርበዋል።

ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) በበኩላቸው ከተማ አስተዳደሩ ላደረገው ድጋፍ አመስግነው በትሕነግ ወራሪው ቡድን የደረሰውን ሰብኣዊ እና ማኅበራዊ ጉዳቶችን በማንሳት በተለይም መሠረተ ልማቶችን እና የኢኮኖሚ አውታሮች ማውደሙን ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ከገጠመው ጉዳት እንዲወጣ እና ማኅበረሰቡን በዘላቂነት ለማቋቋም ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ መጠየቃቸውን ከከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።