በአሸባሪው ሕወሓት የፈረሱ ቤተ እምነቶችን መልሶ ለመገንባት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

ታኅሣሥ 13/2014 (ዋልታ) በአሸባሪው የሕወሓት ቡድን የፈረሱ መስጂዶች እና ቤተ-ክርስቲያናት መልሶ ለመገንባት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር እድሪስ በወቅታዊ አገራዊ ሁኔታ ላይ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር በመግለጫቸው የአሸባሪው ሕወሓት ወራሪ ቡድን በርካታ የሃይማኖት ተቋማት ማውደሙን ገልጸው ኢትዮጵያ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች ሁኔታ እና የደረሰውን ጉዳት የሚያጣራ ኮሚቴ ማቋቋሙን አስታውቀዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ በአማራ እና አፋር ክልል የሚገኙ የሃይማኖት አባቶች እና የአገር ሽማግሌዎች ቤተ እምነቶችን መልሶ ለመገንባት የበኩላቸውን ማድረግ አለባቸው ብለዋል፡፡

በሽብር ቡድኑ ወረራ የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ድጋፍ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በትዝታ ወንድሙ