በምዕራብ ሀረርጌ ዞን ዶባ ወረዳ የተሰሩ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች ተጎበኙ

ታኅሣሥ 13/2014 (ዋልታ) የኢፌዴሪ ግብርና ሚኒስትር ዴኤታ እያሱ ኤሊያስ (ፕ/ር) በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሀረርጌ ዞን ዶባ ወረዳ የተሰሩ የተፋሰስ ልማት ሥራዎችን ጎበኙ።

በዶባ ወረዳ ሰፊ መሬት በተፋሰስ ልማት እየለማ ሲሆን የልማት ሥራዎች የጎበኙት ሚኒስትር ዴኤታው የወረዳ አርሶ አደሮች እየሰሩ ያሉትን አመርቂ ሥራ በማድነቅ መሰል ሥራዎችን በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች በማስፋፋት በአጭር ጊዜ ውስጥ ከምግብ ጥገኝነት እንላቀቃለን ብለዋል።

ምዕራባዊያን ድህነታችንን ተገን አድርገው ሊጠቀሙብን እያንጋጠጡብን ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው እኛ ግን ከጥንትም ጠንካሮች ነንና ለዚህ ፍላጎታቸው አንበረከክምም ብለዋል።

ለዚህም በምዕራብ ሀረርጌ እየተሰሩ ያሉት የተፋሰስ ልማት ሥራዎች ዋነኛ ማሳያዎች መሆናቸውን ገልፀዋል።

በምዕራብ ሀርጌ ከተሰሩ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች ተሞክሮን ለመውሰድ ታቅዶ ከተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ዞኖች የተወጣጡ እንግዶች በምዕራብ ሀረርጌ እያካሄዱ የሚገኙት ጉብኝት የመጀመርያ ዙር ተጠናቆ በዛሬው እለት የሁለተኛ ዙር ጉብኝት እየተካሄደ ይገኛል።

በታምራት ደለሊ