የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ከሜድሮክ ኢንቨስትመንት ጋር የውል ስምምነት አደረገ

ታኅሣሥ 14/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ከሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ጋር የውል ስምምነት አደረገ፡፡

ሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በስሩ ያሉትን ድርጅቶች ጥራትን መሰረት አድርጎ ከመስራት አንፃር የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት በትኩረት እንዲመዝንለትና ወደ ለውጥ ጎዳና ለማሳደግ ያለመ ስምምነት መሆኑን የግሩፑ ማኒፋክቸሪንግ ዘርፍ አቅም ግንባታና ሲስተም ማኔጅመንት ዳይሬክተር ቴዎድሮስ ተሰማ ገልፀዋል፡፡

አገርን ለኪሳራ የሚዳርገውና ዓለም ዐቀፍ ተወዳዳሪነትን የሚቀንሰው ጥራትን ካለመጠበቅ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ ጥራት ላይ ተመርኩዞ መስራት ለአገር እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ተናግረዋል::

ዓለም ዐቀፍ ተፅእኖን ለመመከትና ኢኮኖሚን ለማሳደግ ድርጅቶች ጥራትን ዋነኛ መንገድ አድርገው መስራት እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ ቴዎድሮስ መብራቱ አሳስበዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የራሷ የሆነ በጥራት የምትታወቅበት ምርት እንዲኖራት ጥራትን መሰረት ያደረገ አሰራርን መከተል ይገባልም ተብሏል፡፡
በአመለወርቅ መኳንንት