የማዕድን ዘርፍን ዋና የዕድገት ምንጭ ለማድረግ በቅንጅት እንደሚሰራ ተገለጸ

ታኅሣሥ 15/2014 (ዋልታ) መንግስት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት በሚገባ በመጠቀም የማዕድን ዘርፍን ዋነኛ የእድገት ምንጭ ለማድረግ በጋራ እንሰራለን ሲሉ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የማዕድን ሚኒስቴር የ100 ቀናት ዕቅድ አፈጻጸም ከፕላንና ልማት ሚኒስቴር ጋር ግምገማና ውይይት የተካሄደ ሲሆን በዘርፉ ባለፉት ሶስት ወራት ተጨባጭ ውጤት የተመዘገበበት መሆኑም ተጠቅሷል፡፡
በማዕድን ምርት አቅርቦት በከፊል በከበሩ የጌጣጌጥ ማዕድናት ከዕቅድ በላይ አፈጻጸም ተመዝግቧል፡፡
በኢንዱስትሪ ግብዓቶች እና በሲሚንቶ ምርት እንዲሁም አቅርቦት የነበረውን ችግር በመፍታት በቀን እየተመረተ ያለውን 160 ሺሕ ቶን ወደ 240 ሺሕ ቶን ለማሳደግ በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል፡፡
በዚህም ምርቱ ከነበረበት የ900 ብር ዋጋም ወደ 450 ብር በኩንታል ማውረድ ተችሏል ነው የተባለው፡፡
ከውጭ የሚገባውን የድንጋይ ከሰል ምርት ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ለማምረት የምርትና ፕሮሰሲንግ ፈቃዶችን ለኩባንያዎች ለመስጠት ስራዎች መጠናቀቃቸውም ተነግሯል።
ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ከውጭ የሚገባውን የድንጋይ ከሰል በሀገር ውስጥ ለመተካት ሚኒስቴሩ ያደረገውን ጥረት በአስቸኳይ ወደ ምርት ለማስገባትም መንግስት ሙሉ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡
የማዕድን ሚኒስትር ታከለ ኡማ በማዕድን ዘርፍ የተሰሩ ስራዎች የተሻሉ ቢሆኑም የበለጠ መስራት ይጠበቅብናል ብለው ሚኒስትሯ ለሰጡት ገንቢ አስያየትና ሃሳብ ምስጋና ማቅረባቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል፡፡