ለ3 ኤርትራዊያን የላቦራቶሪ ባለሙያዎች ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ተጠናቀቀ

ታኅሣሥ 15/2014 (ዋልታ) ከኤርትራ ለመጡ 3 ‹‹የኮርማ አባላዘር ላቦራቶሪ ባለሙያዎች›› ለ23 ቀናት በብሔራዊ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ኢንስቲትዩት ሲሰጥ የነበረው የንድፈሐሳብ እና የተግባር ሥልጠና ተጠናቀቀ፡፡
ሥልጠናው በአባላዘር አመራረት፣ የኮርማ እንክብካቤ፣ የአባላዘር ፕሮሰሲንግ እና አያያዝ ላይ ያተኮረ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡
የብሔራዊ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶክተር አስራት ጤራ ሰልጣኞች የቀሰሙትን ክህሎት እና እውቀት በመጠቀም በአገራቸው ላይ ትልቅ ሥራ እንደሚሰሩ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡
ዳይሬክተሩ አክለውም መሰል ሥልጠናዎች የሁለቱን አገራት እህትማማችነት እንደሚያጠናክር ገልጸው ወደ ፊትም የሚቀጥል ነው ማለታቸውን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡