በታላቁ ጉዞ ወደ አገር ቤት የሚጓዙ የዳያስፖራ አባላትን የሚያስተናግድ ዌብሳይት ይፋ ሆነ

ታኅሣሥ 18/2019 (ዋልታ) በታላቁ ጉዞ ወደ አገር ቤት ጥሪ መሰረት ወደ የኢትዮጵያ የሚመጡ የዳያስፖራ አባላትን የሚያስተናግድ ዌብሳይት ይፋ ሆነ።
አንድ ሚሊዮን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላት ወደ ሀገር ቤት እንዲመጡ የቀረበውን ሀገራዊ ጥሪ ተከትሎ በርካታ የዳያስፖራ አባላት ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ እንደሆነ ይታወቃል።
በዚህም ጉዳዩን እንዲያስተባብር በአገር ዐቀፍ ደረጃ የተቋቋመው ኮሚቴ ሴክሬታሪያትና አስተባባሪ የሆነው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ የዳያስፖራውን የቆይታ ጊዜ የተቀናጀ፣ ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ የሚያግዝ እንዲሁም ለዳያስፖራው ሁለገብ መረጃ የሚያቀርብና የዳያስፖራ አባላትን መረጃዎች ለማሰባሰብና ለማደራጀት የሚያስችል ወጥ የሆነ የኦንላይን የመረጃ ድረ-ገጽ አዘጋጅቷል።
የድረ-ገጹ አድራሻም www.greatethiopianhomecoming.org ሲሆን የዳያስፖራ አባላት በድረ-ገጹ register በሚለው ታብ በመግባት በሚያገኙት ፎርም እንዲመዘገቡና ከድረ-ገጹ መረጃዎችን ማየትና ያሏቸውን ጥያቄዎች በመጻፍ ቀጥተኛ ምላሽ ማግኘት የሚችሉ መሆኑን ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።