የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖችን ዳግም ወደ ሥራ ሊመልስ ነው

የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ታኅሣሥ 18/2019 (ዋልታ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖችን ዳግም ወደ ሥራ ለመመለስ ዝግጅቱን እያጠናቀቀ መሆኑንና የመጀመሪያ በረራውን ጥር 24/ 2014 ዓ.ም እንደሚያደረግ አስታውቋል፡፡

የአየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ተወልደ ገብረ ማርያም ደኅንነት የኩባንያው ቀዳሚ ጉዳይ መሆኑን በመጥቀስ አየር መንገዱ 737-ማክስ አውሮፕላኖችን ዳግም ወደ ሥራ ሲመልስም የተለያዩ ሀገራት የአቪዬሽን ቁጥጥር ተቋማት ለአውሮፕላኑ ዳግም የበረራ ፈቃድ ከሰጡ በኋላ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት በዓለም 34 ያህል አየር መንገዶች አውሮፕላኑን ዳግም እየተገለገሉበት እንደሚገኙ ተጠቅሷል፡፡

አየር መንገዱ የቦይንግ 737-ማክስ አውሮፕልንን ለመመለስ ከመጨረሻዎቹ አየር መንገዶች ተርታ እንደሚሆን በገባው ቃል መሰረት የዲዛይን ማሻሻያ ሥራውንና ከ20 ወራት በላይ የፈጀውን ጥብቅ የማረጋገጫ ሂደት ሲከታተል እንደቆየና አብራሪዎች፣ ኢንጂነሮች፣ የአውሮፕላን ቴክኒሻኖች እና የበረራ ባለሙያዎቹ በአውሮፕላኑ እርግጠኛ እስከሚሆኑ ድረስ መጠበቃቸውን ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ አንድ ወር ውስጥም ለተጓዦች ተጨማሪ ዝርዝር መረጃዎችን እንደሚያቀርብ ከአየር መንገዱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡