በአፋር ክልል ተቋርጦ የነበረው የመደበኛ የመንግሥት ሥራ ነገ ይጀመራል

ታኅሣሥ 18/2014 (ዋልታ) የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በክልሉ በአሸባሪው ሕወሓት ወረራ ምክንያት ተቋርጦ የነበረው መደበኛ የመንግሥት ሥራ ነገ እንደሚጀመር የክልሉ የፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሃብት ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡
የቢሮው ኃላፊ መሀመድ አህመድ አሊ በሰጡት መግለጫ የሕወሓት ቡድን በክልሉ ባደረገው ወረራ ባስከተለው ሰብኣዊ እና ቁሳዊ ጉዳት ምክንያት የክልሉ የመንግሥት ሥራ ተቋርጦ መቆየቱን አንስተዋል፡፡
የአፋር ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻ እና የአፋር ሕዝባዊ ኃይል ከጀግናው መከላከያ ሰራዊት ጋር በመሆን ባደረጉት ተጋድሎ ወራሪውን ኃይል ደምስሰዋል ብለዋል፡፡
ስለሆነም የክልሉ መደበኛ የመንግሥት ሥራ ከነገ ማክሰኞ ታኅሣሥ 19 ጀምሮ እንዲጀመር እና የመንግሥት ሰራተኞች በሥራ ገበታቸው ላይ እንዲገኙ ጥሪ መቅረቡን ከክልሉ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡