ወደ አገር ቤት ለሚገቡ ዳያስፖራዎች አቀባበል ለማድረግ በሚያስችለው ሂደት ላይ ውይይት እየተደረገ ነው

ታኅሣሥ 19/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ ወደ አገር ቤት ለሚገቡ ዳያስፖራዎች አቀባበል ለማድረግ በሚያስችለው ሂደት ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያደረገ ይገኛል።

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ዳዊት የሺጥላ ውይይቱ ከተማ አስተዳደሩ አሁን ካለው የትራንስፖርት ፍሰት አኳያ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጥሪ ተቀብለው ወደ አገር ቤት የሚገቡ ኢትዮጵያውያንን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ለመቀበል እያደረገ ባለው ዝግጅት ላይ ትኩረቱን እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የሕዝብ ትራንስፖርትን የተሻለ ከማድረግ ጀምሮ አነስተኛ የተናጥል ትራንስፖርት የሚሰጡ ተቋማት ተአማኒ፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ እና ፈጣን አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ከወትሮው በተለየ መስራት ይገባናል ብለዋል።

ይህንን ለማድረግ የቴክኖሎጂ አሰራሩን በማስተካከል ታማኝነት ያለው እንዲሁም ህጋዊ የስምሪት አገልግሎት መስጠትን ያካትታል ነው የተባለው።

ወደ አገር ቤት የሚገቡ ዳያስፖራዎች በአዲስ አበባ በሚኖራቸው ቆይታ በኢትዮጵያዊነት ትህትና ተቀብለን ቆይታቸው ያማረ እንዲሆን ሁሉም በትብብር መስራት እንዳለበት ተጠቅሷል።