የ122 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ተዘጋጀ

ታኅሣሥ 21/2014 (ዋልታ) ለአገር ደኅንነት ማስጠበቂያ፣ ለሰብአዊ እርዳታ፣ በጦርነትና ግጭቶች ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ማቋቋሚያ እንዲሁም ለሌሎች አስፈላጊ የመንግሥት ስራዎች ማስፈጸሚያ የሚውል የ122 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ተዘጋጀ፡፡

በገንዘብ ሚኒስቴር የተዘጋጀው የ122 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡

ተጨማሪ በጀቱን ማዘጋጀት ያስፈለገው በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተካሄደው ጦርነት ምክንያት ተጨማሪ ወጪ በማስፈለጉ፣ መንግሥት በሚሰበስበው ገቢ አሁን ያለውን የክፍያ ጥያቄ መመለስ አስቸጋሪ በመሆኑ እንዲሁም የተጨማሪ ወጪ ፍላጎትን በበጀት ሽግሽግ ማስተናገድ አዳጋች በመሆኑ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የተጨማሪ በጀት ጥያቄው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወይይት ተደርጎበት እንደ ጸደቀ በቀጥታ ስራ ላይ እንደሚውል የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል::