በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች አሸባሪው ሕወሓት ያቆሸሸውን የቅዱስ ላልይበላን አከባቢ አፀዱ

ታኅሣሥ 21/2014 (ዋልታ) የላስታ ላልይበላ አካባቢ፣ የፍላቂት ገረገራ አካባቢና ከደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ የተውጣጡ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች ‹‹ቅዱስ ላልይበላን በፍላጎቴ አጸዳለሁ›› በሚል መሪ መልዕክት አሸባሪው ሕወሓት ያቆሸሸውን የቅዱስ ላልይበላን አከባቢ አፅድተዋል።

በጎ ፈቃደኞቹ በቀጣዩ ታኅሣሥ 29 ቀን 2014 ዓ.ም የሚከበረውን የልደት በዓልን ምክንያት በማድረግ ወደ ስፍራው የሚመጡ እንግዶችን በጽዱ ከተማ ለመቀበል ታስቦ እንደሆነም ጠቁመዋል።

የላስታ ላልይበላ አካባቢ አስተባባሪውና የሕዝብ ግንኙነቱ ልዑልሰገድ መንገሻ በላልይበላ የሚከበረውን በዓል ምክንያት አድርገው የሚመጡ እንግዶች ጽዱ በሆነች ከተማ ተስተናግደው እንዲሄዱ ፍላጎታቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አካባቢው ከአሸባሪው ቡድን እንደጸዳ ሁሉ ተከታትለው ቆሻሻውን በማጽዳት ላይ ናቸው። በሰላሙ በኩል ምንም አይነት ስጋት እንደሌለ ገልጸዋል።

ከፍላቂትና ገረገራ ወጣቱን አስተባብሮ ከ80 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት ተጉዞ የመጣው ወጣት አንደበት ብርሃኑ በበኩሉ አካባቢው ሰላም መሆኑ ተናግሯል፡፡

ሰሜን ወሎ ሙሉ ለሙሉ ከጁንታው እንደጸዳች ሁሉ አሁን ጁንታው አበላሽቶ የሄደውን ስፍራ ሁሉ በማጽዳት እንግዶችን ለመቀበል መዘጋጀታቸውን አስረድቷል፡፡

በፅዳቱ ላይ ከተሳተፉት የእስልምና እምነት ተከታዩ የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ መምህር አቡበከር ጥላሁን ጁንታው ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ለመከላከያ ሰራዊትና ለጥምር ጦሩ ደጀን በመሆኑ ሲሳተፍ እንደሰነበተ ተናግሯል፡፡

የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ የሳይኮሎጂ ትምህርት ክፍል መምህር አብዮት አለባቸው በበኩሉ ለጥምር ጦሩ ደጀን ከመሆን ጎን ለጎን ኅብረ ብሔራዊ ዘመቻውንም ለመቀላቀል ስልጠና መውሰዱን ጠቅሶ የቆሸሸውን ለማጽዳት በላልይበላ መገኘቱን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ገልጿል፡፡