በላስ ቬጋስ በአንድ ምሽት ከ350 ሺሕ በላይ የአሜሪካን ዶላር ተሰበሰበ

ታኅሣሥ 22/2014 (ዋልታ) በጦርነቱ የተጎዱና የተፈናቀሉ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም በላስ ቬጋስ በተካሄደ ገቢ ማሰባሰበያ ከ350 ሺሕ የአሜሪካን ዶላር በላይ መሰብሰቡ ተገለጸ፡፡

በላስ ቬጋስ የጉዞ ኢትዮጵያ የሀብት አሰባሳቢ ኮሚቴ የሕዝብ ግንኙነት ንዑስ ኮሚቴ አስተባባሪ ተሻገር ከልካይ ዲያስፖራው ድጋፉን በተለያዩ አማራጮች እንዲያስገባ የተደረገበት አካሄድ በመኖሩ ያልተቆጠሩና ያልተካተቱ የሀብት ስብስቦች በመኖራቸው ትክክለኛው ቁጥር አሁን መናገር ባይቻልም በዕለቱ በተካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ መርኃ ግብር ብቻ ከ350 ሺሕ የአሜሪካን ዶላር በላይ ማሰባሰብ ተችሏል ብለዋል።

ከገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪም የመድኃኒትና የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉንም ተናግረዋል።

እንደ አቶ ተሻገር ገለጻ ድጋፉ በአፋርና አማራ ክልሎች ለሚገኙ በጦርነቱ ለተጎዱና ለተፈናቀሉ ዜጎች አፋጣኝ ድጋፍ ለማድረግና ኑሯቸውን በተሻለ ሁኔታ መምራት የሚችሉበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የሚውል ነው።

የአሁኑ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅቱ የአንድ ጊዜ ዝግጅት ብቻ ሳይሆን በቀጣይ ጊዜያትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተጠቁሟል፡፡

እንደ ትምህርት፣ ጤናና መሰረታዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ወደነበሩበት ሁኔታ እንዲመለሱ ለማድረግና ከመላው ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን የጠላትን ሴራ በማክሸፍ ኢትዮጵያ ወደተሻለ እድገት እንድትራመድ ለማስቻል የበኩላቸውን እንደሚወጡም ተሳታፊዎቹ ቃል መግባታቸውን የኢፕድ ዘገባ ያመለክታል።