ከ84 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የኮንትሮባንድ እቃዎች ተያዙ

ታኅሣሥ 23/2014 (ዋልታ) ባሳለፍነው ሳምንት ከ84 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የገቢና የወጭ የኮንትሮባንድ እቃዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ ባሳለፍነው ሳምንት ባደረገው ክትትል 78 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር የገቢ ኮንትሮባንድ እቃዎች እና 5 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የወጪ ኮንትሮባንድ እቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ተይዘዋል።

የገቢ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር ረገድ ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዙት ሞያሌ፣ ድሬዳዋ እና ጅግጅጋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች ሲሆኑ በቅደም ተከተላቸው 18 ሚሊዮን 998 ሺሕ፣ 18 ሚሊዮን 987 ሺሕ ሚሊዮን እና 17 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎችን መያዝ ችለዋል።

የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኞች፣ በፌደራል ፖሊስ፣ በክልል ፖሊስ አባላትና ኅብረተሰቡ ባደረጉት የጋራ ጥረት በፍተሻና በጥቆማ የተያዙ ሲሆን የኮንትሮባንድ እቃዎቹን ሲያዘዋውሩ የተገኙ ሶስት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውም ተጠቁሟል፡፡

በቁጥጥር ስር ከዋሉት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል አልባሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድኃኒት፣ የመዋቢያ እቃዎች የጦር መሳሪያዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ እጾች እና የተለያዩ ሀገራት ገንዘቦች ይገኙበታል፡፡

የጉምሩክ ኮሚሽን በዚህ የህግ ማስከበር ስራ ላይ ለተሳተፉ የኮሚሽኑ ሰራተኞች፣ የክልልና የፌዴራል ፖሊስ አባላት ምስጋና ማቅረቡን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።