የሲዳማ ክልል ምክር ቤት ጉባኤ አዋጆችንና ሹመቶችን በማፅደቅ ተጠናቀቀ

ታኅሣሥ 23/2014 (ዋልታ) የሲዳማ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 1ኛ የሥራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ጉባኤ የተለያዩ አዋጆችንና ሹመቶችን በማፅደቅ ተጠናቀቀ።

የምክር ቤቱ ጉባኤ የክልሉን የመንግሥት ሰራተኞች መተዳደሪያ ደንብ አዋጅ እንዲሁም የክልሉን የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን መልሶ ለማደራጀት እና የከተሞችን አደረጃጀትና የሥልጣን ደረጃ ለመወሰን የወጡ አዋጆችን አፅድቋል።

በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ አማካኝነት የቀረቡትን እመቤት ኢሳያስ የክልሉ የሴቶች፣ ወጣቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አድርጎም መሾሙን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በተጨማሪ ተሻለ ዩኒ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ እንዲሆኑ ምክር ቤቱ ሹመታቸውን ተቀብሎ አጽድቋል።

ጉባኤው እስከ ታኅሣሥ 24 ይቀጥላል ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም አንድ ቀን ቀድሞ ለምክር ቤቱ የተለያዩ ቋሚ ኮሚቴዎች የሰብሳቢና ምክትል ሰብሳቢዎች ሹመትን በማፅደቅ ተጠናቋል፡፡