የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እጩ ኮሚሽነሮች አቀራረብ ሥርዓት ተዘረጋ

አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

ታኅሣሥ 25/2014 (ዋልታ) የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እጩ ኮሚሽነሮች አቀራረብ ሥርዓት በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መዘርጋቱን አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ተናግረዋል፡፡

የእጩ ኮሚሽነሮችን ጥቆማ የሚቀበልና የሚያደራጅ የጥቆማ ተቀባይ ኮሚቴ መቋቋሙም ታውቋል፡፡

ኮሚቴው የእጩ ኮሚሽነሮችን ጥቆማ ከመቀበል ጀምሮ በምክር ቤቱ ቀርበው እስከሚሾሙበት ድረስ የተለያዩ ተግባራትን እንደሚያከናውን ተገልጿል፡፡

የጽህፈት ቤቱ ሰብሳቢ ሄኖክ ስዩም (ዶ/ር) እና ሌሎች ሁለት አባላትም በኮሚቴው መካተታቸውን አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ አስታውቀዋል፡፡

የምክክር ኮሚሽኑ እጩ ኮሚሽነሮች ጥቆማ አቀባበል አሳታፊ፣ ግልጽ፣ ተዓማኒና ከአድሎ የጸዳ እንዲሆን ለማስቻል የሚያግዝ የአማካሪ ቡድንም ተቋቁሟል፡፡

የአማካሪ ቡድኑ በአፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ የሚመራ ሲሆን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት፣ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ተወካይ እንዲሁም የሲቪክ ማኅበራት ጥምረት ተወካይ በአባልነት ተካተውበታል፡፡

አማካሪ ቡድኑ የተለያዩ ተግባርና ኃላፊነት የተሰጡት ሲሆን ከቀረቡ እጩዎች ውስጥ በአዋጁ ላይ የተቀመጡትን መስፈርቶች በከፍተኛ ደረጃ የሚያሟሉትን እጩዎች በመለየት ረገድ አፈ ጉባኤውን ማማከር ዋነኛው ስለመሆኑ ዛሬ በተደረገው ውይይት ተጠቁሟል፡፡

የጥቆማ መስጫ መርኃ ግብርና ጥቆማ የሚሰጥበት ፎርማት ገና ይፋ ሳይደረግ ጥቆማዎች እየቀረቡ ስለመሆኑ አፈ ጉባኤው ገልጸው ነገር ግን እነዚህ ጥቆማዎች ተቀባይነት እንደማይኖራቸው አስታውቀዋል፡፡

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እጩ ኮሚሽነሮች ማቅረቢያ ጊዜ፣ ፎርማትና አጠቃላይ የእጩዎች አቀራረብ ሥርዓትን በተመለከተ አፈ ጉባኤው ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጡ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡