በምስራቅ ወለጋ ዞን ዲጋ ወረዳ 10 የአሸባሪው ሸኔ አባላት ተማረኩ

የአሸባሪው ሸኔ አባላት

ታኅሣሥ 26/2014 (ዋልታ) በምስራቅ ወለጋ ዞን ዲጋ ወረዳ በተለምዶ ጅርማ ክላስተር በሚባል መንደር በተካሄደ ኦፕሬሽን በአካባቢው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 10 የሸኔ አባላት ተማረኩ፡፡

አባላቱ ዘመናዊና ኋላ ቀር የጦር መሳሪያ ታጥቀው ሕዝብን በማሸበር በዘረፋ ተሰማርተው የነበሩ ሲሆን አርቴፊሻል የጦር መሳሪያዎችን ጭምር በመያዝ ንፁሓንን በማስፈራራት ለዝርፊያ ሲጠቀሙ እንደነበረ ተገልጿል፡፡

የዞኑ የፀጥታ ኃይል በአካባቢው ባካሄደው ኦፕሬሽን 7ቱ ሲማረኩ የተቀሩት ሶስት የሽረተኛ ቡድኑ አባላት ከፀጥታ ኃይሉ ሊያመልጡ እንደማይችሉ በመገንዘብ ለአባ ገዳ እጅ ሰጥተዋል ተብሏል፡፡

የከተማረኩት የሽብር ቡድኑ አባላት አሸባሪው ሸኔ እንዲዘርፉ፣ መረጃ እንዲያቀብሉ እና ቤት እንዲያቃጥሉ ያደራጃቸው ኃይሎች እንደሆኑም ነው የተገለፀው፡፡

ሆኖም በዞኑ በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች በአስተማማኝና በወሳኝ መልኩ ኦፕሬሽኖች በመካሄድ ላይ ሲሆን ጠላት በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች በሙሉ እየተመታ እየተበታተነ መሆኑን የምስራቅ ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ አለማየሁ ተስፋ ገልፀዋል፡፡

አሸባሪው ሸኔ የተቆጣጠራቸው አካባቢዎች በሙሉ በዞኑ የፀጥታ ኃይል ቁጥጥር ስር እየገባ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በደረሰ አማረ